አብዝተን እናጭድ ዘንድ አብዝተን እንዝራ! (በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!! አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከ347 እስከ407 ዓ.ም. የነበረና ከ398 እስከ 404ዓ.ም. የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ ሆኖ ያገለገለ ታላቅ የቤተክርስቲያንአባት ነው፡፡ ይህ አባት ከሚያስተምረው የትምህርቱ ጣዕም የተነሣ “አፈወርቅ፣ ጥዑመ ልሳን” ተብሏል፡፡በእርግጥም በትምህርቱ ሁሉንም መማረክ የሚችል፤ ለማንም የማያዳላ ይልቁንም ለድሆች ጠበቃየሚሆንላቸው የፍትሕ አባት ነው፡፡ ትምህርቶቹም ዘመን ተሻጋሪና ክርስቲያናዊ ሕይወቱን መመዘን ለሚፈቅድሰው የማያዳሉ ሚዛኖች ናቸው፡፡ እስኪ ዛሬም በዚያ አንደበቱ ይናገረን፤ እኛም እንደ ሊድያ ልቦናችንንከፍተን እንስማው፤ ከዚያም ራሳችንን እንመርምር፡፡
ወንድሞቼ ሆይ! ወደ ቤተ ክርስቲያን ውድ ስጦታዎችን ይዛችሁ ስትመጡ አያለሁ፡፡ መልካም አድርጋችኋል፡፡ነገር ግን ስትመለሱ ደግሞ መበለቶችን፣ ደሀ አደጎችንና ሕጻናትን ስትበድሉ አያችኋለሁ፡፡ ታድያ ይህን ሁሉእያደረጋችሁ በወርቅ የተንቆጠቆጠ ምሥዋዕና ጽዋዕ ብታቅረቡ ምን ይጠቅማችኋል? ለምንስ መሥዋዕቱንማክበር ስትፈልጉ አስቀድማችሁ ልባችሁን መባ አድርጋችሁ አታቀርቡም? ልባችሁ በጭቃ ተጨማልቆምሥዋዑ እንኳን ወርቅ ፕላቲንየምስ ቢሆን ምን ይረባችኋል? ምንስ ይጠቅማችኋል?
ተወዳጆች ሆይ! አመጣጣችን በወርቅ የተለበጠ መሠዊያ ለማቅረብ ሳይሆን ይኸን ከልብ በመነጨ ለማቅረብይሁን፡፡ ከልባችን የምናቀርበው ነገር ሁሉ ከወርቅ የበለጠ መባ ነው፡፡ ልብ በሉ! ቤተ ክርስቲያን የወርቅወይም የነሐስ ማቅለጫ ቦታ አይደለችም፤ ለቅድስና የተጠሩ ሁሉ እና የመላእክት ኅብረት እንጂ፡፡ ስለዚህከስጦታችሁ በፊት ልባችሁን ይዛችሁ ኑ፡፡ እግዚአብሔር እኮ ሥጦታችንን የሚቀበለው ደሀ ሆኖ ሳይሆን ስለነፍሳችን ብሎ ነው፡፡ ክርስቶስን ማክበር ትወዳላችሁን? እንግዲያስ ዕራቆቱን ስታዩት ችላ አትበሉት፡፡ እናንተወደ ቤተ መቅደስ ስትመጡ እጅግ ውድ በሆኑ ልብሶች አጊጣችሁ ስትመጡ እርሱ በብርድና በመራቆትሊሞት ነውና ብያንስ ትንሽ እንኳን እዘኑለት፡፡ ቤተ መቅደስ ረግጣችሁ ቤተ መቅደስ አትምጡ፡፡ በቃሉ “ይህሥጋዬ ነው” ያለው ጌታ በተመሳሳይ ቃሉ “ተርቤ ስታዩኝ አላበላችሁኝም፤… ከሁሉ ከሚያንሱትከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም” ይለናል /ማቴ.25፡42፣45/፡፡በእውነት ይህ ምሥዋዕ ልብሳችሁን ሳይሆን ልባችሁን ነው የሚፈልገው፤ እነዚህ የተራቡት ግን ልብስምምግብም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህ በሕይወታችን ክርስቶስ እርሱ እንደሚወደው ማክበርን እንማር፡፡ እከብርአይል ክቡር የሆነው እርሱ ደስ የሚያሰኘው ክብር እኛ ውድ ነው ብለን የምናቀርበው ሳይሆን እርሱሊቀበለው የወደደውን ስናቀርብለት ነው፡፡
ጴጥሮስ ጌታን ያከበረ መስሎት እግሩን መታጠብ እምቢ አለ፤ ይህ ግን በጌታ ዐይን ማክበር ሳይሆን ተቃራኒውነበር፡፡ ስለዚህ ጌታን ማክበር ስትፈልጉ ገንዘባችሁን አስቀድማችሁ በድሆች ላይ አውሉት፡፡ ምክንያቱም እርሱየሚፈልገው ወርቃማ ምሥዋዕን ሳይሆን ወርቃማ ነፍሳትን ነው፡፡ ይህን ሁሉ የምላችሁ ግን መባ እንዳትሰጡእየከለከልኳችሁ አይደለም፤ ይልቁንም ከዚሁ ጐን ለጐን እንደውም አስቀድማችሁ መመጽወትንእንድትለማመዱ ነው እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ለምሥዋዑ ያመጣችሁትን መባ ይቀበላል፤ ለድሆች የምትሰጡትንደግሞ ከዚሁ በበለጠ ይቀበላችኋል፡፡ ለምሥዋዕ የሚሆን ወርቅ ብታመጡ ተጠቃሚዎች እናንተ ብቻ ናችሁ፤ለድሆች ስትሰጡ ግን ድሀውም እናንተም ትጠቀማላችሁ፡፡ ለምሥዋዕ የሚሆን ወርቅ ስትሰጡ ውዳሴ ከንቱሊያመጣባችሁ ይችላል፤ ለድሆች ስትሰጡ ግን ርኅራኄንና ሰው ወዳድነትን ያመጣላችኋል፡፡ ጌታ ተርቦ ሳለምሥዋዑ በወርቅ ቢንቆጠቆጥ ምን ጥቅም አለው? ከሁሉም በፊት ጌታ ተርቦ ስታገኙት አብሉትና ከዚያምምሥዋዑን አስጊጡት፡፡ ነገር ግን እርሱ አንድ ኩባያ ውኃ እንኳን ሳያገኝ እናንተ ጽዋውን የወርቅ ጽዋታደርጉታላችሁን? እርሱ ገላውን የሚሸፍንባት ቁራጭ ጨርቅ እንኳን አጥቶ እናንተ ምሥዋዑን በወርቅ ልብስታስጌጡታላችሁን? ከዚሁ የምታገኙት መልካም ነገርስ ምንድነው? እስኪ ንገሩኝ! እርሱ የሚበላውን ዳቦአጥቶ እናንተም ረሀቡን ሳታስታግሱለት ወደ ቤተ መቅደሱ መጥታችሁ ምሥዋዑን በብር ስታስጌጡትየሚያመሰግናችሁ ይመስላችኋልን? ንገሩኝ እንጂ? የማይቆጣችሁስ ይመስላችኋልን? እንደገና አንድ ሰውቁራጭ ጨርቅ ለብሶ ብርድ ሲያቆራምደው እየተመለከታችሁ ምንም ልብስ ሳትሰጡት በቤተመቅደስመጥታችሁ “ይህ ሥጦታ ለጌታዬ ክብር ነው” ብላችሁ ምሥዋዑን በወርቅ ብታስጌጡት ጌታ፡- “ፌዘኞች!”ብሎ እንደሰደባችሁት የማይቈጥረው ይመስላችኋልን?
እርሱ መጠለያ ፈልጐ እንግዳና መንገደኛ ሆኖ ሲዞር እናንተ ግን ባለ ብዙ ክፍል ቤት እያላችሁ ችላብላችሁታል፡፡ ቤታችሁ በተለያዩ የመብራት ዓይነት አጊጦ ሳለ ክርስቶስ ግን በእስር ቤት ነው፤ ልታዩትእንኳን አልወደዳችሁም፡፡ ወንድማችሁ በጣም ተቸግሮ እያያችሁት እናንተ ግን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንንለማስጌጥ ትሮጣላችሁ፤ ነገር ግን አማናዊው ቤተ መቅደስ ከሕንጻው የበለጠ ወንድማችሁ ነበር፡፡ ወንድሞቼ!ልንገራችሁና እናንተም አድምጡኝ! ለሕንጻው ቤተ መቅደስ የምታመጧቸው ጌጣጌጦች አንድ ኢአማኒ ንጉሥ፣ወይም ጨካኝ መሪ፣ ወይም ሌባ ሊዘርፋቸው ይችላል፡፡ ወንድማችሁ ሲራብ፣ እንግዳ ሆኖ ሲመጣ እናሲታረዝ የምታደርጉለትን ማንኛውም ነገር ግን እንኳንስ ጨካኝ መሪ፣ እንኳንስ ጨካኝ ሌባ የጨካኞች አባትየሆነው ዲያብሎስም መውሰድ ይቅርና ሊያይባችሁም አይችልም፡፡ ገንዘባችሁ ሁሉ በአስተማማኝ ቦታይከማቻል፡፡ ምጽዋት የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ ትከፍታለች፡፡ “ጸሎትህ እና ምጽዋትህ ለመታሰብያእንዲሆን ዐረገ” እንዲል /ሐዋ.10፡4/፡፡ ምጽዋት ከመሥዋዕት ሁሉ የበለጠች መሥዋዕት ናት፡፡“ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፣ ከሚቃጠለውም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማውቅእወዳለሁ” እንዲል /ሆሴ.6፡6/፡፡ ምጽዋት ኃጢአትን ታነጻለች፡፡ “የሚወደድ ነገርስ ለምጽዋት ስጡ፤ሁሉም ንጹሕ ይሆንላችኋል” እንዲል /ሉቃ.11፡41/፡፡ እንግዲያስ አብዝተን እናጭድ ዘንድ አብዝተንእንዝራ፡፡ ይህን ሁሉ እንድናደርግና የሚመጣውን ዓለም እንድንወርስ ሰውን በማፍቀር ሰው የሆነው ጌታችንናመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን፡፡ አሜን!!
የወላዲተ አምላክ ረድኤትና በረከት አይለየን:: አሜን!
እመቤታችን ከማረፏ ከሰዓታት በፊትና በኋላ ምን ሆነ?
ማርያም ስጋኪ ዘተመሰለ ባሕርየ
ተሓፍረ ሞት አኮኑ ሶበ ነጸረ ወርእየ
እንዘ በደመና ብሩህ የዐርግ ሰማየ
እንኳን አደረሰን
እመቤታችን በእናት አባቷ ቤት ሦስት ዓመት፣ አሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ /ዘጠኝ ወር በቤተ ዮሴፍ/፣ ከመድኃኒታችን ጋርሰላሣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ፣ በቤተ ዮሐንስ አሥራ አምስት ዓመት፤ ጠቅላላ ስድሳ አራት ዓመት በዚህ ምድር ኑራለች::
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ለአገልግሎት ወደ ኤፌሶን በሄደበት ወቅት የቤተ መቅደስ አለቆች ልጆች የነበሩ ደናግል እግሯን እያጠቡ እየተላላኩ ያገለግሏት ነበር:: እመቤታችን ጐልጐታ በሚገኝው የመቃብር ቦታ እየሄደችም አዘውትራ ትጸልይ ነበር:: መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም በመቃብሩ በምትጸልይበት ጊዜ ከዚህ ዓለም በሥጋ ስለምታርፍበት ሁኔታ ከነገራት በኋላ ታመመች:: ያን ጊዜ አገልጋዮቿና ጎረቤቶቿ ሁሉ በአንድነት ተሰበሰቡ ብዙ ድውያንም ወደእርስዋ እየመጡ ያመሰግኗትና ይፈወሱም ነበር:: እመቤታችንም ደስ ብሏት ትባርካቸዋለች::
የዓለምን አልጫነት በወንጌል ጨውነት ያጣፍጡ ዘንድ ለአገልግሎት የወጡ ክቡራን ደቀ መዛሙርትም እመቤታችን ከማረፏ በፊት በረከትን ሊቀበሉና በክብር ሊያሳርፏት ተሰበሰቡ :: ከመላእክትም ጋር በአንድነት ቅድስት ቡርክት ወደሆነች እመቤታችን ቤት ገቡ:: ከእግሯ በታችም ሰገዱ “ጸጋን ፍጹም ደስታን የተመላሽ ሆይ ሰላምታ ለአንቺ ይገባሻል ፣ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ሆይ አትደንግጪ :: ከአንቺ የተወለደው ክርስቶስ በታላቅ ምስጋና ከዚህ ዓለም ሊለይሽ ፣ ወደብርሃን ቤቶችም ሊወስድሽ ነውና ” እያሉ ያረጋጓጓት ነበር::
እመቤታችን ማርያምም ተነሥታ “እኔ እንደታመምሁ የነገራችሁ ማን ነው? ከየትስ አገር ወደ እኔ መጣችሁ? በምን ተጭናችሁስ ፈጥናችሁ ደረሳችሁ? ስለ እኔ የነገራችሁን እግዚአብሔርን ላመሰግን እወዳለሁ ” አለቻቸው:: ቅዱስ ጴጥሮስም “እያንዳንዳችሁ ወደዚህ እንዴት እንደመጣችሁ ንገሯት” አላቸው::
አስቀድሞ የመጣ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ አለ:: “በኤፌሶን ሳለሁ መንፈስ ቅዱስ ወደ እኔ መጣ:: ዮሐንስ ሆይ የጌታህ እናት ከዚህ ዓለም የምትለይበት የዕረፍቷ ዕለት ደርሷልና ሒድ ፤ ልታይህም ትሻለች አለኝ:: ዳግመኛም መንፈስ ቅዱስም በሀገሮች ሁሉ እሔዳለሁ ፤ ለሐዋርያትም ለሕያዋኑም፣ ለሙታኑም እነግራቸዋለሁ ፤ ወደ ቤተልሔም ወደርሷ ይሔዱ ዘንድ ይሳለሟትም ዘንድ ስለ ማርያም እነግራቸዋለሁ አለኝ:: እነሆም መንፈስ ቅዱስ በደመና በድንገት ነጠቀኝ :: በዚህች ሰዓትም ከማርያም ዘንድ አደረሰኝ::” በማለት መሰከረ:: የቀሩትም ሁሉ በድንቅ አጠራሩ ስቦ ያቀረባቸው መሆኑን መሰከሩ:: ሉቃስ ወንጌላዊ ፣ ስምዖን ቀነናዊና እንድርያስ የተጠሩበት አጠራርም እጅግ ያስደንቅ ነበር :: ከመቃብር ተጠርተው ነበርና:: መላእክትም ከእነርሱ ጋር ነበሩ::
ቅዱሳን ሐዋርያት ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ ከእለታት ሁሉ በምትከብር በእለተ ሰንበት “ከዚህ ዓለም እናቱን ይወስዳት ዘንድ በእርሷ ላይ ክብሩን ይገልጣል” እንዳላቸው ሆነ:: የሰው ልጆች ሁሉ እናታቸው ሔዋን፣ የእመቤታችን እናት ሐና ፣ ቅድስት ኤልሳቤጥ “የክብሩ ማደርያ ትሆኝ ዘንድ የመረጠሽ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን አሏት::” ፤አባታችን አዳም ፣ ልጁ ሴት ፣ ኖኅ ፣ ሴም ፣ አብርሃም ፣ ይስሐቅ ፣ ያዕቆብ ፣ ዳዊት ፣ የእሳት ማእጠንት የያዙ ሌሎችም ነቢያት ከእመቤታችን ፊት ሰገዱ ፤ ሄኖክና ሙሴም በእሣት ሰረገላ ተጭነው መጡ ፤ቁጥራቸው የብዙ ብዙ የሚሆን የከበሩ መላእክት ከዚህ ዓለም የማርያምን መለየት ያዩ ዘንድ መጡ :: ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኪሩቤልና በሱራፌል ሰረገላ ተቀምጦ ተገለጠ:: እናቱንም ጠርቶ የሰማያትን ምስጢር ሁሉ አሳያት :: የሲዖልና የገነት ነፍሳትን ሁሉ ጎበኘች:: መታሰቢያዋን ለሚያደርጉ ፣ በስሟ መሥዋዕት ለሚያሳርጉ ሁሉ ቃል ኪዳን ከተቀበለች በኋላ በጥር ሃያ አንድ ቀንም ዐረፈች::
የከበረ ወንጌላዊ ዮሐንስ እጆቿን አነሣ አቃናት፤ ዓይኖቿንም ከደነላት ፤ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስም እጆቿንና እግሮቿን አስተካከሉ:: በእርሷ ላይ ያለውን ልብሷን ግን አላወጡትም፤ መንፈስ ቅዱስ የማይመረመር ታላቅ ብርሃናዊ ልብስን አልብሷታልና:: የከበረ ሥጋዋን በጌቴሴማኒ ሊያሳርፉ ቅዱሳን ሐዋርያትና የተወደዱ የክርስትያን ወገኖች ተሰብስበው ሳለ፤ ለክፋት የማያርፉ አይሁድ ተነሱባቸው:: “በድነ ሥጋዋን እንወስዳለን እናቃጥላለንም ” አሉ::
ታውፋንያ የተባለ ጭፍራም ልከው የእመቤታችንን ሥጋ የያዘውን አልጋ እንዲጥል እጁን በዘረጋ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ በእሳት ሰይፍ መታው፤ ሁለት እጆቹንም ከትከሻው ቆረጣቸው አልጋውም ላይ ተንጠለጠሉ:: ታውፋንያም አለቀሰ ፤ ወደ ሐዋርያትም ጮኽ፤ ሐዋርያትም አልጋዋን ትስብባት ዘንድ የወደድህ ማርያምን ለምናት አሉት:: “ እናቴ ማርያም ሆይ ይቅር በይኝ ” አለ:: እመቤታችንም እጆቹ ይመለሱለት አለች:: በቅዱስ ጴጥሮስም “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ፤ ቅድስት በሆነች በማርያምም ስም እንደነበራችሁ ሁኑ ” ሁኑ አላቸው:: በዳነ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ አለው “ እመቤታችን ማርያም በአንተ ላይ ያደረገችውን ለአይሁድ ንገራቸው፤ እነርሱ እመቤታችንን ይሰድቧታልና ፤ በሕይወቷ አሸንፋናለች ፤ ዛሬ ግን እኛ ሥጋዋን እናቃጥላለን ብለዋልና ” አለው::
ከዚህ በኋላ ልአከ እግዚአብሔር የከበረ ሥጋዋን ሰውሮ በአጸደ ገነት አኖረው:: ይህ ምስጢር የተገለጠለት ጌታውን ይወድ የነበረ ደቀ መዝሙር ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ የነገራቸውን ለማየትና ሥርዓተ ቀብሯን በሚገባ ባለማድረጋቸው ሲያዝኑ ኖረዋልና ምስጢር ተከፍሎባቸው እንዳይቀር ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው በያዙት ሱባዔ “ ሞት በጥር ነሐሴ መቃብር ” እንዲሉ በነሐሴ አሥራ አራት ቀን የከበረ ሥጋዋ ተሰጥቷቸው በታላቅ ጸሎትና ዝማሬ ቀብረዋታል::
ለአገልግሎት ሩቅ አገር ሂዶ የቆየው ሐዋርያው ቶማስ ከዚህ ታላቅ ምስጢር ተለይቼ እያለ ደመና ጠቅሶ በታላቅ ሐዘን ወደ ሐዋርያት ሲመጣ እመቤታችን እንደልጇ ባለ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ተመለከተ:: ምስጢር ተከፍሎበት የመሰለው ቶማስ ሲያዝን ፤ የመጀመሪያው የወላዲተ አምላክ ትንሣኤ ምስክር መሆኑን ተረዳ:: የትንሣኤዋን ዜና ያበስር ዘንድም የመግነዟን ጨርቅ ምልክት እንዲሆነው ሰጠችው::
ከሐዋርያት ሲደርስም የሆነውን አጫወቱት :: ይህ እንዴት ይሆናል? አላቸው:: ቀድሞ የጌታህን ትንሣኤ ተጠራጥረህ ተገስጸህ ነበር:: አሁን የእናቱን እረፍት እየነገርንህ ትጠረጥራለህን? አሉት:: መቃብሯን አሳዩኝ ብሏቸው ሊያሳዩት ወደጌቴሴማኒ በሄዱ ጊዜ መቃብሩ ባዶ ሆኖ አገኙት:: ቶማስም የሆነውን እንድታምኑ እንጅ እኔስ ጠራጥሬ አይደለም :: በማለት የምሥራች አላቸው:: በዚህም ታላቅ ደስታን አደረጉ:: ከዚያን ጊዜ ወዲህም በኦርቶዶክስ አቢያተ ክርስትያናት ሁሉ ዘንድ ከሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ከትውፊት እንዳገኝነው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የፍልሰቷ፣የትንሣኤዋና የዕርገቷ በኣል መጽሐፋዊ ፣ትውፊታዊና ማኅሌታዊ በሆነ ሥርዓት፤ በጾምና በጸሎት በሱባዔም የሚከበር ታላቅ በኣል ነው::
የጌታችን ክህነትና የመልከ ፄዴቅ ክህነት
ቅዱስ ጳውሎስ ለምን ጠቀሰው? - - - ዕብ.3:1 “ስለዚህ፥ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ” ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ በእብራውያን መልእክቱ ያተኮረው ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁሉ የሚበልጥ መሆኑን ማስረዳት ነው፡፡ ይህንንም የሚያስረዳው ደግሞ በንፅፅር ነው፡፡ ከነቢያት ስለመብለጡ የእነሱን ንግግርና የእሱን ንግግር በማነፃፀር አስረዳ፡፡ ከዚያም በኅላ ደግሞ ከመላእክት መብለጡን አስረድቷል፡፡ አሁን ደግሞ ከካህናት መብለጡን ለማስረዳት ያመጣል፡፡ ከካህናት መብለጡንም ሲያስረዳ ዋናወቹ ምክንያቶች 1) በክህነቱ 2) በመስዋእቱ 3) መስዋእቱ በቀረበበት ድንኳን መሆኑን ያስረዳል፡፡ ስለክህነቱም በ ዕብ.5፡1-10 ፣ በዕብ. 6፡20 ፣ 7፡1-28 ፣ 8፡1-3 ባሉት አስረድቷል፡፡
ክህነት ምንድን ነው? - - - አገልግሎት ሲሆን መሾምን መመረጥን ያመለክታል፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስም ከአዳም ጀምሮ የተለያዩ ሰወች ለዚህ ክህነት በሰውም በእግዚአብሄርም ሲመረጡ ያሳየናል፡፡
መልከ ፄዴቅ ማነው? - - ዕብ.7:3 “አባትና እናት የትውልድም ቍጥር የሉትም፥ ለዘመኑም ጥንት ለህይወቱም ፍጻሜ የለውም፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።” ይህ ሲባል መልከ ፄዴቅ ሰው አይደለም ማለት አይደለም ፡ ዘሩ ከካም ዘር ነበረና በሙሴ መፃህፍት አልተገለፀም ለማለት ነው፡፡ ይህ የተመረጠ ሰው አፅመ አዳምን እንዲጠብቅ የታዘዘ በብህትውና የሚኖር ነው፡፡ የመልከ ፄዴቅ ክህነትም ሙሴ አሮንን በሾመበት ሥርአት ቅብዕ አፍልቶ ፡ መስዋእተ እንስሳ ሰውቶ ፡ልዩ ልዩ ህብር ያላቸውን አልባሳት አልብሶ የሾመው ሰው የለም፡፡ይልቁንም እግዚአብሄር መረጠው ፡ በማይታወቅ ግብርም ሾመው እንጂ፡፡ አሮንና ልጆቹ በሙሴ እጅ ፡ ሙሴም በመልአኩ እጅ እንደተሾሙ (ሐዋ ፡ 6፡6) መልከፄዴቅ ግን ሹመቱ ከእግዚአብሄር ነውና ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ “ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል።” ያለው ለዚህ ነው፡፡ “ለዘላለም” ማለቱም እስከ ህይወቱ ፍፃሜ ማለቱ ነው፡፡በዚህም ምክንያት ክህነቱ ከሌዋውያን ክህነት ፍፁም የተለየ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ እንደሌዋውያን ክህነትም የእንስሳት መስዋእት አይሰዋም መስዋእቱ ንፁህ ስንዴና ወይን ነውንጂ፡፡ በዚህም ተነስቶ ቅዱስ ጳውሎስ - - ዕብ.7:11 እንግዲህ ህዝቡ በሌዊ ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን፥ እንደ አሮን ሹመት የማይቈጠር፥ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሳ ወደፊት ስለ ምን ያስፈልጋል? ብሎ ይጠቅሰዋል፡፡
ነገር መልከ ፄዴቅ በእብራውያን - - -
- የሌዋውያን ካህናትን በክህነት ይቀድማቸዋል እርሱ ከአብርሃም በፊት ነበረና --- ዘፍ 14፡18-21
- ክህነቱ ዘላለማዊ ነው - ዕብ 7፡3 ለብዙ ዘመናት በብህትውና እንደኖረና ክህነቱም ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ስላልሆነ ይህ ተጠቅሷል፡፡ የሌዋውያን ክህነት ግን ሞት በየጊዜው አለባቸውና ዕብ.7:23 “እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው” እንዲል፡፡
- ሌዋውያንን አስራት አስወጥቷል - - - ሌዋውያን ከህዝቡ አስራትን እንዲቀበሉ ስርአት አላቸው፡፡ ነገር ግን መልከ ፄዴቅ ከአብርሃም አስራትን በተቀበለ ጊዜ ከእነርሱ ክህነት የእርሱ ክህነት እንዲበልጥ ታወቀ፡፡
- ሌዋውያንን ባርኳል - - - እጃቸውን ዘርግተው ህዝቡን የሚባርኩት የሌዋውያን ካህናት በአብርሃም በኩል በመልከ ፄዴቅ ተባርከዋል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ዕብ.7:6-7” ትውልዱ ከእነርሱ የማይቈጠረው ግን ከአብርሃም አሥራትን አውጥቶአል፥ የተስፋ ቃል የነበረውንም ባርኮአል።ትንሹም በታላቁ እንዲባረክ ክርክር የሌለበት ነገር ነው።”እንዲል፡፡
- መስዋእቱ የሚሞቱ እንስሳት አይደሉም - - - የሌዋውያን ካህናት መስዋእታቸው ከእንስሳት የሚዘጋጅ ሲሆን የመልከፄዴቅ መስዋእት ግን ከንፁህ ስንዴና ወይን የሚዘጋጅ ነው ፡፡ ይህም የክርስቶስ ስጋውና ደሙን የሚያመለክትልን ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉንም በዚህ ምእራፍ አጠቃልሎ እንዳስቀመጠው ክህነተ መልከፄዴቅ ክህነተ ሌዋውያንን ይበልጣል፡፡ የጌታችን የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክህነት ደግሞ ከመልከ ፄዴቅ ክህነት ይበልጣል፡፡ መልከፄዴቅ ለጌታችን አምሳል ነበርና፡፡ ስለዚህ የቅዱስ ጳውሎስ ንግግር አባታችሁ አብርሃም አብርሃማዊ ካልሆነው ከመልከ ፄዴቅ የሚያንስ ከሆነ ይልቁንም ከመልከ ፄዴቅ አምላክ ከክርስቶስማ እንዴት አያንስም? የመልከ ፄዴቅ ክህነት ከእናንተ ከተሻለ ይልቁን የጌታማ እንዴታ! መስዋእታችሁ ከመልከ ፄዴቅ ካነሰ ይልቁን እንዴት ከጌታ ትበልጣላችሁ ፣ ለመልከ ፄዴቅ አስራት ካወጣችሁ ለጌታማ እንዴት አብዝታችሁ ማድረግ አይገባችሁ? በመልከ ፄዴቅ ከተባረካችሁ ይልቁንም መስጠትና መንሳት ለእርሱ ብቻ ከሚቻለው ከወልደ እግዚአብሄርማ እንዴት አብልጣችሁ መጠቀም ይገባችኅል ለማለት ተናገረው፡፡አላማውም የጌታን ታላቅነትና የባህርይ አምላክነት በመመስከር ልቆ ከሚልቁት እነርሱንም ያላቃቸው እርሱ መሆኑንና ይህ ስልጣን እንዳለው ለማስታወቅ ነበር፡፡
የጌታችን ክህነት በምን የተለየ ሆነ? - - -
- የባህርይው ስለሆነ - - - ክርስቶስ ሁሉንም ነገር ያደረገው በስልጣኑ ነው፤ ሙትን ያስነሳው ድውያኑን የፈወሰው ፡ ያስተማረው ፡ የሞተው ፡ የተነሳው ፡ ያረገው ፡ - - - በስልጣኑ ነው፡፡ የጌታችን የክህነት አግልግሎት ዋናው ራሱን በመስቀል ላይ መስዋእት አድርጎ ማቅረቡ ነው፡፡ ይሄውም ስጋውን ቆርሶ ፡ ደሙን አፍስሶ ፡ ነፍሱን ክሶ አለሙን የመቀደስና የማንፃት ሞትንና የሞትን አበጋዝ ዲያቢሎስን በሞቱ ድል መንሳቱ ነው፡፡ ይህ ነው የጌታችን ከእርሱ ለእኛ የተደረገልን የክህነት አገልግሎት፡፡ ሞቱ ደግሞ በስልጣኑ እንደሆነ ሞቱን በስልጣኑ ፈፀመው መባሉ ደግሞ ክህነቱ የባህርይው መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ ከማንም አልተቀበለውም ፡ ማንምም ከእርሱ አይወስድበትም፡፡ይህም ማለት ባህርይ መለኮቱ ባህርይ ትስብእቱን በተዋህዶ አከበረው እንጂ ሌላ የሚሰጠው እርሱም የተቀበለው የለም፡፡ ስለዚህ እርሱ እንደመልከፄዴቅ በስውር እንደ አሮን በገሃድ የተሾመ አይደለም ፡ እርሱ ሰጪ እንጂ ተቀባይ አይደለምና፡፡ዮሐ 1፡3 “ሁሉ በእርሱ ሆነ” እንዲል፡፡ ዕብ.5:5 “እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም ነገር ግን። አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው” ሲል የቃልን በስጋ መወለድ ሐዋርያው ተናግሯል፡፡ ይህም በእርሱ ፈቃድ ብቻ ሳይሆነ በአባቱም ፈቃድ መሆኑን ለመናገር ነው፡፡
- ዘላለማዊ ነው - - - “ዘላለም” የሚለው ቃል ለፍጡርና ለፈጣሪ ሲቀፅል አንድ እንዳልሆነ አንባቢ ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህም የመልከፄዴቅ ክህነት ህይወቱ እስኪያልፍ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ የጌታችን ክህነት ዘላለማዊነቷ እርሱ ሽረትና ሞት የሌለበት አምላክ ስለሆነ ነው፡፡ በስጋ ሞተ የምንለውም ነፍሱ ከስጋው ተለየች ለማለት እንጂ ከተዋህዶ በኅላ መለኮትና ትስብእት የተለያዩበት ቅፅበት የለም፡፡ስለዚህ ለክህነቱ ተቀባይ አያስፈልገውም ፡ የባህርይ ክህነትም ከእርሱ በቀር ገንዘብ ሊያደርገው የሚቻለው የለምና፡፡ ዕብ.7:24 “እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው” ተብሎ ተፅፏልና፡፡ዕብ.7:24-25 “እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።” - - - እነዚህ ጥቅሶች ጌታችንን “አማላጅ” ነው በማለት የሚያስተላልፉት መልእክት የለም፡፡ የሰው ልጆች ሁሉ በክርስቶስ ቤዛነት አምነው ሲመጡ የእግዚአብሄር ቤተመቅደስ ሆኑ የሚባሉት በስመ ስላሴ ተጠምቀው የክርስቶስን ስጋና ደም ሲቀበሉ ብቻ ነው፡፡ የክርስቶስ ስጋና ደም ደግሞ እንደ ኦሪት መስዋእት በአንድ ቀን የሚያልቅ ፡ በጊዜ ብዛት የሚለውጥ ፡ የሚበላሽ አይደለም ፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ አዲስና ለዘላለሙ በህይወት የሚኖር ነው፡፡ “ሕያው” መባሉም ነፍስ ስለተዋሃደው ሳይሆን “መለኮት” ስለማይለየው ነው፡፡ - - - ይህ ሕያው ስጋውና ደሙ ሁልጊዜ ሰውን ወደ እግዚአብሄር ሲያቀርብ የሚኖር ከእግዚአብሄርም ጋር የመታረቂያው ብቸኛ መንገድ በመሆኑ አማለደን (አስታረቀን) ሲል ገልፆታል፡፡ “ሊያማልድ በህይወት ይኖራል” የሚለውንም በጥሬ ንባቡ ከሆነ ጌታችን አሁንም በስጋ ህይወት በምድር አለ ያስብልብናልና፡፡
- ፍፁም ነው - - - የሌዋውያን ክህነት ፍፁም አይደለም ፤ የመልከ ፄዴቅም ዘላለማዊ እንጂ (አንፃራዊ) ፍፁም አልነበረም፡፡ ማንንም ወደ ገነት መመለስ አልተቻላቸውምና፡፡ እነርሱም ራሳቸው በአዳም የመጀመሪያ ሃጢአት ተይዘዋልና፡፡ “እርሱ ራሱ ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ” ዕብ 7፡28 ፣ ዕብ 5፡2 ተብሎባቸዋልና፡፡ ለጌታችን ግን ሃጢአት የለበትም ተብሏል፡ 1ኛ ዮሐ3፡5 ከዚህ የተነሳ ክህነታቸው ፍፁም አይደለም፡፡በመሆኑም እለት እለት ወደ ቤተ መቅደስ እየገቡ የሚሞት መሥዋእት ማቅረብ ግድ ሆነባቸው፡፡ ዕብ 9፡6-7 እርሱ ግን ክህነቱ ፍፁም መሥዋእቱም ህያው ስለሆነ እለት እለት መስዋእት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ ዕብ.7:27 “እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።” እንዳለ አንድ ጊዜ ባቀረበው መስዋእት ለዘላለም አንፅቶን ሊኖር ይቻለዋልና፡፡ ቆላ.1:19-20 “እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና።”እንዲል
ታዲያ የጌታችን ክህነት በመልከ ፄዴቅ ክህነት ለምን ተመሰለ?
“የነገር ጥላ አለውና” ዕብ 10፡1 እንደ ተባለ ለሰው ረቂቁን በግዙፉ ፡ የሚታየውን በማይታየው መስሎ መናገርና ማስረዳት የተለመደ ነው፡፡ ይልቁንም እኛ የሰው ልጆች ከህሊናት በላይ የሆነውን እግዚአብሄርን መረዳት የቻልነው በምሳሌ ነው፡፡ ክርስቶስም ሲያስተምረን አብዛኛውን ጊዜ በምሳሌ ነበር፡፡ በዚህም አንፃር መልከ ፄዴቅ የወልደ እግዚአብሄር ምሳሌው እንጂ ራሱ እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆን ይገባል፡፡ ምሳሌ የሆነውም መልከ ፄዴቅ ብቻ አልነበረም ፦ዮናስ ምሳሌ ሆኖ ተጠቅሷል ማቴ 16፡4 ፣ ሙሴ በምድረ በዳ የሰቀለው እባብ ዮሐ 3፡14 ፣ ሙሴ ዉሃን ያፈለቀበት ዐለት 1ኛቆሮ 10፡1 እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ምሳሌወችም አሉት፡፡ በመልከ ፄዴቅ የመሰለበት ምክንያትም
የመልከ ፄዴቅ እናትና አባት በእብራውያን ዘንድ የታወቀ እንዳልሆነ የጌታችን ለቀዳማዊ ልደቱ እናት ለደሃራዊ ልደቱ አባት የለውምና
መልከ ፄዴቅ በስንዴ በወይን ያስታኩት ነበረ ፤ ጌታም ቅዱስ ስጋውን በስንዴ ክቡር ደሙን በወይን አድርጎ ሰጥቶናልና
መልከ ፄዴቅ በዚህ ጊዜ ተገኝ በዚህ ጊዜም አለፈ አይባልም ፤ ጌታም በዚህ ጊዜ ተገኝ በዚህ ጊዜም ያልፋል አይባልም፡፡ እና ሌሎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ጌታችን ስለምን ሊቀካህናት ተባለ?
ከላይ በመልከ ፄዴቅ እንደተመሰለ አሁን ደግሞ በኦሪት ሊቀ ካህናት ተመስሏል፡፡ ስለ ምን? ስለጌታችን ክህነት የመልከ ፄዴቅ ምሳሌነት ያልገለጠው ነገር አለ ፤ ይሄውም አገልግሎቱ ነው፡፡ ጌታችንም ሊቀ ካህናቱን ምሳሌ ያደረገው ከዚህ አገልግሎቱና ከአለቅነቱ አንፃር ነው፡፡ ይሄውም ፦
- ሊቀ ካህናት ከሰው ተመርጦ ለሰው ይሾማል - - - ዕብ.5:1 “ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መስዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና” እንዲል፡፡ ሊቀ ካህናት ሰው ነው ፡ ከሰው ይመረጣልና የሚሾመውም ለሰው እንጂ ለራሱ ክብር አይደለምና፡፡ ጌታችን ክርስቶስም ፍፁም አምላክ ሲሆን ፍፁም ሰው ነው፡፡ የአብርሃም ልጅ የዳዊት ልጅ ተብሏልና፡፡ማቴ 1፡1 ሊቀ ካህናት ስለሰው እንደሚሾም ጌታችንም ሰው የሆነውና ክህነትን ገንዘብ ያደረገው ስለ ሰው ነው፡፡ የሰውን ሃጢአት ለማራቅ ሰው ሆኗልና፡፡ዮሐ.3:16-17 ”በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።” 1ጢሞ.1:15 “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ” እንደተባለ፡፡
- ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት የሚችለው ሊቀ ካህናት ብቻ ነው - - - ይህንንም በዘሌ16፡2 የተጠቀሰውን ቅዱስ ጳውሎስ ዕብ.9:6-7 “ይህም እንደዚህ ተዘጋጅቶ ሳለ፥ ካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤ በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፥ እርሱም ሰለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ስሕተት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤” በማለት በማያሻማ ሁኔታ ገልፆታል፡፡ ጌታችንም የገባባት ቅድስተ ቅዱሳን በሰው ያልተተከለች በፈቃደ እግዚአብሄር የሆነች ከእርሱም በፊት ከእርሱም በኅላ ማንም ያልገባባትና የማይገባባት ናት፡፡ ሊቀ ካህናት በአመት አንድ ጊዜ ይገባል ፡ እርሱ ግን አንድ ጊዜ ብቻ ገባ ፤ ለዓለምና ለዘላለም መስዋእቱ ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ እነዚያ በየዓመቱ የሚገቡት ሟች ስለሆኑ መስዋእታቸውም ሙት ነውና ሌላ አዲስ ያስፈልጋቸዋል፡፡ዕብ.9:11-12 “ ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥ የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም።” ተብሎ ተፅፏል፡፡ ጌታችን የገባባት ድንኳን የተባለችው “መስቀል” ናት፡፡ ድንኳን ያላት የዘላለም መስዋእት የሆነው የጌታ ቅዱስ ስጋ የተቆረሰው ክቡር ደሙም የፈሰሰው በመስቀሉ ላይ ስለሆነ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ወደዚች ድንኳን “አንድ ጊዜ ፈፅሞ በገዛ ደሙ ወደ ቅድስት ገባ” በማለት ራሱን መስዋእት አድርጎ የወጣበት መስቀል መሆኑን በግልፅ አስረድቷል፡፡ “በሰው ያልተተከለች” ሲልም አይሁድ መስቀሉን ጌታን ለመግደል እንጂ መስዋእተ እግዚአብሄር ይቀርብበታል ብለው ስላልሆነ ነው፡፡ “ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች” ማለቱም በመስቀል ላይ እራሱን መስዋእት ሊያደርግ የሚችል ሰው የለም ፤ ቢኖርም እንኳ ሌላውን ራሱን ማዳን አይቻለውምና ፡ ለፍጥረት ባልሆነች ብሏታል፡፡
- ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መስዋእትን ሊያቀርብ ይሾማልና ዕብ 8፡3 -- -- የሊቀ ካህናት ዋናው አገልግሎት መባንና መስዋእትን ማቅረብ ነው፡፡ ጌታችንም የዓለምን ሃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሄር በግ የተባለበት ዮሐ1፡29 ራሱን መስዋእት አድርጎ ያቀረበ ብቸኛ ሊቀ ካህን ነው፡፡ ራሱ መስዋእት በመሆኑም ሌላ የሚያቀርበው መስዋእት አላስፈለገውም፡፡ ሁለቱንም አንድ ጊዜ መሆን ይቻለዋልና፡፡ ዕብ.9:12 “የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም።” ዕብ.10:12 “እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ” እንዲል፡፡ ዕብ.9:26 “- - - አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።” የተባለው ለዚህ ነው፡፡ ዕብ.8:1-3 “ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ይሾማልና፤ ስለዚህም ለዚህ ደግሞ የሚያቀርበው አንዳች ሊኖረው የግድ ነው።” እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ “በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን” ሲለን የትሩፋተ ስጋ የትሩፋተ ነፍስ ጀማሪ በልእልና ሃይል ባለው እሪና የተቀመጠ አስታራቂያችን ነውና ስለዚህ ተናገረ አንድም የዚህ ሁሉ ደገኛ ነገሩ ሊቀ ካህናታችን በልእልና ሃይል ባለው እሪና የኖረው መኖርን ይገልፃል፡፡ “እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።” የተባለውበሰው ፈቃድ ያይደለ በእግዚአብሄር ፈቃድ በተተከለች በደብተራ መስቀል ራሱን መስዋእት ፡ መስዋእት አቅራቢውም ራሱ ደግሞም መስዋእቱንም ተቀባይ ራሱ ሆኖ ለቅዱሳን ሲያገለግል ኑሮ ነበር፡፡ የክርስቶስ መስዋእትም “ሕያው” ማለትም ለዘላለም የሚኖር ሲሆን እንደ ሌሎቹ ሊቀ ካህናት መስዋእት አንድ ጊዜ ተዘጋጅቶ ቶሎ የሚበላሽ ስለዚህም እለት እለት መስዋእት ማቅረብ የሚገባበት አይደለም፡፡ የቀደሙት ሊቀካህናት በሰው በተተከለችው ቅድስተ ቅዱሳን በአመት አንድ ጊዜ መስዋእትን ሊያቀርቡ እንደሚገቡ ያይደለ ለክርስቶስ ግን በእግዚአብሄር በተተከለች ደሙን ባፈሰሰባት ፡ ስጋውን በቆረሰባት ፡ ነፍሱን ካሳ አድርጎ በሰጠባት እውነተኛይቱ መቅደስና ድንኳን በተባለች በመስቀል አንድ ጊዜ ፈፅሞ ገባ ማለት ተሰቀለ፡፡ መስዋእቱን ያቀረበው ክርስቶስ የቀረበው መስዋእት የክርስቶስ ክቡር ስጋው ቅዱስ ደሙ ስለሆነ መስዋእት አቅራቢው እንደሌሎቹ ሊቀካህናት በራሱ ህፀፀ የለበትምና መስዋእቱም የሚበላሽ ፡ የሚሞት ፡ የሚበሰብስ እንደሆነው የቀደመው መስዋእት አይደለምና ነገር ግን ነገር ግን ለዘላለም የሚኖር ክርስቶስ ራሱን መስዋእት አድርጓልና የማስታረቁ ተግባር ፍፁም ነው፡፡ እርሱም ክህነቱ ፍፁም መሥዋእቱም ህያው ስለሆነ እለት እለት መስዋእት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ይህንን አንድ ጊዜ ፈፅሞ አድርጓልና፡፡ ክቡር ደሙና ቅዱስ ስጋውም ለዘላለም አምነውና በስላሴ ስም ተጠምቀው የሚመጡትን ሰወች ከሃጢአታቸው አጥቦ የዘላለም ህይወትን ሊያወራሳቸው ይችላል ማለት ነው፡፡ አንድም ዘወትር (አሁንም) መስዋእትን በሰማይ ያቀርባል ካልን እለት እለት በሰማያት ክርስቶስ ወደ እውነተኛይቱ ድንኳን (መስቀል) ይወጣል ማለት ይሆንብናል (ይህም ይሰቀላል ማለታቸን ነው) - - - ደግሞም የክርስቶስ መስዋእት እንደሌሎቹ ሊቀ ካህናት መስዋእት ድካም አለበት ፍፁም አይደለምና አንድ ጊዜ የሰዋው መስዋእት አልበቃውም ማለት ይሆንብናል፡፡ - - - ሌላም ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሰዋው መስዋእት ሙሉውን የሰው ልጅ እዳ በደል አላቀለለም ማለት ይሆንብናል፡፡ ይህም ሊባል አይገባም ክርስቶስም አንድ ጊዜ ባቀረበው መስዋእት ሰውን ሁሉ ይቅር ብሏል ፡የማስታረቅንም ተግባር ፈፅሟል በሰማያትም በአባቱም ቀኝ ተቀምጧል ይህም መቀመጡን እንጂ ለአገልግሎት መቆሙን አያሳይም፡፡ ክርስቶስም ለሃዋርያቱ እንደተናገረ ውደ አባቴ የምሄደው አሁን እንዳደረኩ ስለሃጢአታችሁ ላማልድ አይደለም ይልቁንም ልፈርድ እንጂ በማለት ማማለድን በምድር እንደፈፀመው በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀምጦም የሚፈርድ እርሱ እንደሆነ አስቀድሞ ተናገረን፡፡ ይህንንም ዮሐ.16:26 “በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም” ብሎ አስረግጦ ተናገረ፡፡
በአጭር ቃል ጌታችን ሊቀ ካህናት ሊባል የተገባው ፍፁም ሰው መሆኑን ለማጠየቅ በእውነተኛይቱ ሰው በማይገባባት ቅድስተ ቅዱሳን (መስቀል) አንድ ጊዜ ብቻ ስለገባ ፡ በእርሷም እውነተኛውን መስዋእቱን (ራሱን) ስላቀረበና ሃጢአተ አለምን ስላራቀ ነው፡፡ የቀደመው ክህነት ግን ፍፁም አይደለም፡፡በመሆኑም እለት እለት ወደ ቤተ መቅደስ እየገቡ የሚሞት መሥዋእት ማቅረብ ግድ ሆነባቸው፡፡ ዕብ 9፡6-7 ጌታችን ግን ክህነቱ ”ፍፁም” መሥዋእቱም “ህያው” ስለሆነ እለት እለት መስዋእት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ ዕብ.7:27 “እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።” እንዳለ አንድ ጊዜ ባቀረበው መስዋእት ለዘላለም አንፅቶን ሊኖር ይቻለዋልና፡፡ ምንጭ፦ “ሁለቱ ኪዳናት” በእብራውያን መልእክት ትርጓሜ ላይ የተመሰረተ
የአብ ፍቅር የወልድ ቸርነት የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡
ቅድስት ዘሠኑይ
በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 23 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሃዱ አምላክ
ጸልዩ ከምቅድመንባበ ዝንቱ ክርታስ
“ይኄይሰኒ ሕገ አፉከ እምአእላፍ ወርቅ ወብሩር ወይጥእም እመዐር ወሶከር - ከብዙወርቅና ብር የአፍህ ህግ ይሻለኛል፡፡ እንደ ስኳርና እንደ ማር ይጥማልና፡፡” በሚጥምአንደበቱ ጌታ አክብሮ አንደበቱን ያጣፈጠለት ዜመኛ የሰኞ ቅድስት ድርሰቱንሲጀምር ባዜመበት ቃል ጀምረን “ንጉሰ ሰላም ሰላመከ ሀበነ - የሰላም ንጉሷ ሰላምህንስጠን” ብለን እኛም ከእርሱ ጋር በማዜም በተሰጠን ሰላም ከዛሬ የድርሰቱን አንዳንድቃላትን እንላለን፡፡
ዛሬ ቅዱስ ያሬድ ስለ ቤተክርስቲያን ቅድስናና በውስጧም ስላለን ስለእኛ በምስጋናመቀደስ ከሞላ ጎደል በድርሰቱ አስቀምጧል፡፡ ይህችን ቤተክርስቲያን አሁን እዚያውሆኜ በአባቴ ዜማ እየቀደስኳት ከእርሷ እራስ ከሆነው አምላካችን ቅድስናን ባገኝእወድ ነበር፡፡ በዚያ ባልሆንም በተሰጠኝ ኃይል መጠን ግን እዚህም ሆኜ ቢሆንከአባቴ ጋር ማመስገን ነፍሴ ትሻለችና ከእናንተ ጋር ይኸው ጀመርን፡፡
“ነአኩተከ እግዚኦ አምላክነ - የቀን ጠባቂ ሌሊትን የምታኖረን በኪሩቤል ላይ ያለህወደ ታች የምታይ አቤቱ አምላካችን እናመሰግንሀለን፡፡” እንደተናገርኩት አባታችንሁለተኛ የጾሙን ሰኞ በምስጋና ጀምሮታል፡፡ ትናንት ቅድስት ያላትን ቅዱሳን ሁኑምያለንን በቅድስና ጎዳና በምስጋና ሕይወታችሁን አድሱ እንጂ በማማረር አምላክንአታሳዝኑት ሲለን ነው፡፡
ይቀጥልና “ነያ ጽዮን ቅድስት . . . መድሐኒት ቅድስት ጽዮን ሆይ ነይ ቅድስት ጽዮንሆይ ነይ በሰማይ ያለህ አባታችን ምስጋና ይገባሀል” እያለ የአባቷ ልጅ ለሆነችውቤተክርስቲያን ጽዮንም እንዲሁ ምስጋናን ወደ ላይ ወደ አርአያም ይልካል፡፡
“ነግሀ ሰላመ ሃበነ . . . - ነጋ በጠዋትም ሰላምህን ስጠን በደስታ እና በፀሎትእንዋል፡፡” ቀን ዛሬ ለእኛ የተሰጠች የእግዚአብሔር ፀጋ ናት፡፡ ይህችንም ስጦታከእርሱ ጋር በመነጋገር እንጂ እንደ ከንቱ ሰው አፍን ባለመከልከል እንዳንውልከጠዋት ጀምሮ ቀኔን ሁሉ በፀሎት ካንተ በሚሆን ደስታ እውል ዘንድ ስጠኝ፡፡ “ደስያለው እርሱ ይዘምር” ያዕ 5÷13 በደስታ በዜማ በሆነ ፀሎት ቀኑን አሳልፍ ዘንድፍቀድልኝ ይላል ዜመኛው ደስታውን በዜማ እያሳለፍን፡፡
“ዓይ ይእቲ ዛቲ እንተ ታስተርኢ . . . ይህች ከሩቅ እንደ ብርሃን የምትታይ እንደፀሐይ የምታበራ ማን ናት? ቅድስት ሀገርን ሙሴ አያት እዝራም ተናገረላት ዳዊትምዘመረላት፡፡” ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን ከሩቅ አይተው ዘመን ተሻግረው “ያቺ”ብለው ተመለከቷት፤ ተነበዩላት፤ ዘመሩላት፤ ቅዱስ የሆነው ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስራሷ ሆኗልና እንደ ጸሐይ ብሩህ ሆና ተገላጠችላቸው፡፡
በውስጧ ያሉትም ስለዚህ ነገር ከቤተክርስቲያን ከራሷ ጋር እንዲህ እያሉ በዜመኛውቋንቋ እንዲህ ያመሰግናሉ፡፡ “ርእዩ ዘከመ አፍቀረነ ወሐረየነ … ተመልከቱእንዳፈቀረን፤ እንደመረጠን፤ ለዓለም ሁሉ መድሃኒት በእንጨት መስቀል የተሰቀለውክርስቶስ አስቀድሞ መረጠን፤ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ስትል ታመሰግነዋለች፡- ቃልህበእውነት ጣፋጭ ነው፡፡ ስለ ሐጥአን የተሰቀልህ ለአህዛብ ታበራለህ፡፡ ፅልመትንየምታስወግድ ብርሃንን የምትሰጥ አእምሮን የምታረጋጋ ከእኔ ዘንድ ያለውንአስቀድመህ ታውቃለህና የእያንዳንዱን ጸሎት ትሰማለህና ለእያንዳንዱም ፍላጎቱንታድርግለታለህና ወደ አንተ የጸለየውን ስማ፡፡” እንግዲህ የዛሬ ምስጋናው ሁሉቅድስት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡
ሊቁ ይቀጥላል፡- “ዘአኮ ፀሐይ ዘያበርህ ለኪ መዐልተ…- በቀን ፀሐይ የሚያበራልሽአይደለሽም፡፡ በሌሊትም ጨረቃ የሚያበራልሽ አይደለሽም፡፡ ብርሃንሽ እርሱእግዚአብሔር ነው፡፡ ጨረቃሽ አይጨልምም፤ ፀሐይሽም አይጠልቅም፤ መሰረትሽምአይናወጥም፤ የመለኮት ማደሪያ ድንኳን፡፡”
አቤት ሊቁ ያዜማል! “ሁሉን ሲችል ታገሰ፤ ስለ ሰዎች ፍቅር ተሰቀለ፤ ያድነን ዘንድነፍሱን ስለእኛ ሰጠ፤ በመስቀሉ ተቤዠን፤ ለቤተ ክርስቲያን በጥምቀትወልዶናልና፡፡” በጥምቀት ለቤተክርስቲያን ልጆች አድርጎ የሰጠን አባት አባትእንደሌለው ልጆች አልተዋችሁም ብሏልና ከጠላታችን ገድሎ ሳይሆን ሞቶ፤ ተዋግቶሳይሆን ተወግቶ፤ ሰቅሎ ሳይሆን ተሰቅሎ ልጅነታችንን አፀናው፡፡
ስለዚህ ሊቁ ቀጠለ “ንጊስ ቤተክርስቲያን . . . ወደ ቤተክርስቲያን እንገስግስ፡፡አቤቱ አንተ ምስጉን ነህ ብላ ስታመሰግን እኛን ከእንቅልፋችን አነቃኸን ሰላምንሰጠኸን ብርሀንንም አቀዳጀኸን፡፡” በሞተ ሥራ ሳለን እኛን እንደምትፈርሰውየብሉይ ኪዳን ቤተመቅደስ ሳይሆን በደምህ ዘላለማዊ አድርገህ ወደ ሰራሀትቤተክርስቲያን በጠዋት በልጅነት አንቅተህ በንስሀ አድሰህ ለምስጋና በሰላምጠራኸን፡፡
እንዲህ እያለ ይመጣና ይህን ሁሉ የምላችሁ ይላል ሊቁ ዘመኑ የጾም የመታረቅ ዘመንነውና ፆሙን በቅድስት ቤት በቅድስና ታሳልፉት ዘንድ የማይመቻችሁ ደግሞ እንደዳንኤል መስኮታችሁን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ከፍታችሁ የቅድስናን ነገር ትሰሩ ዘንድነው፡፡ “እስመ በጾም ወበጸሎት ወበምፅዋት ይድኀኑ . . . በጾም በጸሎትና በምፅዋትከሞት ይድናሉ፡፡ ወደ መንግስተ ሠማያት ይደርሳሉ ለንስሀ ፆምን ለሰጠን ለአብለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል፡፡” ግቡ ይህ ነው፡፡
“በጾም ወበጸሎት . . . በፆም በፀሎት በምልጃ በስግደት በእምነት ወደ ፊቱእንቅረብ፡፡” በእምነት ያለን በዚህ ወቅት በፆም እና በፀሎት በስግደትም በእርሱ ፊትልንቀርብ ያስፈልጋል፡፡
“. . . እስመ ተፋጥኑ ገቢረ ሰናየ . . . መልካምን ለመስራት ቸኩሉ፡፡” የፆም ነገርበጎ ህይወትን በጎ ሥራን ሁሉ ማበርታት ማሳደግ ነውና ፆም ብቻውን ሳይሆን ከበጎሥራ ጋር ያዙ ይላል ዜመኛው፡፡
በአባቴ ሰላምታ እንደጀመርኩ እንደ እርሱ እያዜምኩ በእርሱ ሰላምታእጨርሳለሁ፡፡ “በተፋቅሮ ነሀሉ ኩልነ . . . ሁላችንም በመፋቀር እንኑር፤ ለሁሉምራሳችንን ዝቅ እናድርግ፤ ወገቡን ታጥቆ ራሱን ዝቅ አድርጎ ሰላምን አድርጎልንና፡፡”በዚህ ሰላም አምላክ ጠብቆ በቅድስናም እርሱን መምሰልን ያጎናፅፈን፡፡
ደካማ ስሆን ስላልተገባኝ ነገር ስለፃፍኩ ስለ እኔ ጸልዩልኝ አሜን፡፡ በጾሙ ሰላምንይስጠን ጾሙን በሰላም ያስፈጽመን በረከቱን ያሳድርብን አምላክ ቅዱስ ያሬድይጠብቀን፡፡
“መምህር ሆይ! አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነኽ” /ዮሐ.፩፡፶/
በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ኅዳር ፳፯ ቀን፥ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የምታውቅ ነፍስ ሐሴት ታደርጋለች፡፡ ክርስቶስን፡- “አንተ መምህረ እስራኤል ነኽ፤ አንተ ንጉሠ ሰማይ ወምድር ነኽ” ትሏለች፡፡ ይኸውም እንደ ፊሊጶስ ማለት ነው /ዮሐ.፩፡፶/፡፡ ይኽቺ ነፍስ ሐሴትን የምታደርገው ግን በነቢብ ብቻ አይደለም፤ በገቢርም ጭምር እንጂ፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ክርስቶስን ታውቁታላችሁን? እንኪያስ ትእዛዛቱን ጠብቁ፡፡ ክርስቶስን የሚያሳዝን ገቢር እየፈጸምን እንደምን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ማድረግ ይቻለናል?
አንድ እንግዳ ወደ ቤታችን ሲመጣ ቤታችንን እንደምን እንደምናሰናዳው ኹላችንም እናውቀዋለን፡፡ ኹላችንም እንግዳችንን ደስ የሚያሰኘው ነገር ለማድረግ የምንቻኰል አይደለንምን? ለእንግዳችን የኾነ ነገር ባናደርግለት፥ እንግዳችን በመምጣቱ ደስ ተሰኝተን እርሱን ደስ የሚያሰኝ ነገር ባናደርግለት፥ ግን ደግሞ በመምጣቱ ደስ እንደተሰኘን ብንነግረው እንግዳችን በፍጹም አያምነንም፡፡ በእንግዳችን መምጣት ደስ እንደተሰኘን ከቃላት ባለፈ በገቢር መግለጥ አለብንና፡፡ እንኪያስ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕይወታችን ከመጣ ደስ መሰኘታችንን በገቢር ልንገልጽ ያስፈልጋል፡፡ እንግዳችን ክርስቶስን የሚያስቈጣ ነገር ልንፈጽም አይገባንም፡፡
እንግዳ ሲመጣ ቆሻሻ ልብስ አይለበስም፡፡ እንግዳ ሲመጣ የሚያስጸይፍ ነገር አይነገርም፡፡ ክርስቶስ በሕይወታችን ውስጥ እንዲኖር ስንፈልግም ቆሻሻ ልብሳችንን (ማንነታችንን) አውልቀን ልንጥል ያስፈልጋል፤ አስጸያፊ ነገራችንን ልንተው ያስፈልጋል፡፡ እንግዳ ሲመጣ ቤት ያፈራው ኹሉ ይቀርብለታል፡፡ ክርስቶስ ወደ ቤታችን ሲመጣም የሚበላ ነገር ልናቀርብለት ይገባል፡፡ ለመኾኑ የክርስቶስ መብል ምንድነው? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይኽን ጥያቄ ሲመልስልን እንዲኽ ብሏል፡- “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” /ዮሐ.፬፡፴፬/፡፡ እንኪያስ ክርስቶስ የራበው ይኸው ነውና እንመግበው፤ ኢየሱስ የጠማው ይኸው ነውና እናጠጣው፡፡ እርሱም ይቀበለናል፡፡ አንዲት ኩባያ ቀዝቃዛ ውኃ ብንሰጠው እንኳ ይቀበለናል፡፡ ስለብዛቱ ሳይኾን ስለፍቅሩ ብሎ ይቀበለናል፡፡ እኛን ስለመውደዱ ይቀበለናል፡፡ የምንወደው ሰው የሰጠነውን የሚቀበለን ስለ መጠኑ አይደለም፤ ስጦታው የወዳጅ ስለኾነበት እንጂ፡፡ ሰው ወዳጁ ጌታም ኹለት ሳንቲም ብንሰጥ እንኳ ብዙ እንደሰጠን አድርጐ ይቀበለናል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስጦታችንን የሚቀበለው ድኻ ስለኾነ አይደለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የድኻውም የባለጸጋውም ስጦታ እኩል የሚቀበለው ስለ ልቡናችን ኀልዮት (Intention) እንጂ ስለ ስጦታው ትልቅነት ወይም ዋጋ አይደለም፡፡ ስለዚኽ ክርስቶስን እንደምንወደው ለመግለጽ የግድ ብዙ ወይም በውድ ዋጋ የተገዛን ስጦታ መስጠት አያስፈልገንም፡፡ ስጦታችን እርሱ ወደ እኛ ስለመጣ ደስ የመሰኘታችን መግለጫ ነውና ስለ ስጦታችን መጠን ልንመለከት አይገባም፡፡
ተወዳጆች ሆይ! ክርስቶስ ስለ እኛ ብሎ እስከምን ድረስ እንደመጣ ለብዉ (አስተውሉ)፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ብሎ አርአያ ገብርን ነሥቶ መጥቷል፤ ስለ እኛ ብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷል፤ ከዚኽ ኹሉ በኋላ እንኳን ሊቀ ካህናችን ነውና እኛን መንከባከቡ አላቋረጠም፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖስ ሲመክር፡- “እግዚአብሔርበእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን” ብሏል /፪ኛ ቆሮ.፭፡፳/፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “አባታችን! ክርስቶስን የሚጠላ ማን አለ?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ ልጆቼ! እርግጥ ነው በቃል ወይም በኀልዮት ደረጃ ኹላችንም ክርስቶስን እንወደዋለን፡፡ ፍቅር የሚገለጠው ግን በቃል ብቻ አይደለም፤ በገቢርም ጭምር እንጂ፡፡ እልፍ ጊዜ እንደምናፈቅር ብንናገር፥ ግን ደግሞ የማናፈቅር ከኾነ ከማንም ይልቅ ምስኪኖች ነን፡፡ በእግዚአብሔርስ ፊት ይቅርና በሰው ፊትም ሞገስ የለንም፡፡ እግዚአብሔርን እንደምናምን በቃል ብንናገር፤ ነገር ግን በገቢር ብንክደው የማይጠቅም ብቻ አይደለም፤ ጉዳትም አለው፡፡ እንኪያስ ተወዳጆች ሆይ! እግዚአብሔርን ማመናችን በቃልም በገቢርም ይኾን ዘንድ እማልዳችኋለኹ፡፡ ክርስቶስን በዚኽ ሰዓት ካልካድነው እርሱም በመጨረሻይቱ ቀን አይክደንምና፡፡ በዚኹ ሰዓት በቃልም በገቢርም በሰው ፊት ብንመሰክርለት እርሱም በመጨረሻይቱ ቀን በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርልናል /ሉቃ.፲፪፡፰-፱/፡፡ ይኽን እንድናደርግ በቸርነቱም ርስቱን መንግሥቱን እንዲያወርሰን ሰውን በመውደዱ ሰው የኾነው ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!